በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2017 ዓ.ም የበጋ ወቅት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች ላይ መደበኛ እና ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲቱዩት አመለከተ።
ኢንስቲትዩቱ የ2016/17 የክረምት ወቅት ትንበያ ግምገማ እና የ2017 ዓ.ም የበጋ ወቅት የአየር ሁኔታ ትንበያ ይፋ ማድረጊያ መድረክ አካሂዷል።
ይህም የሚሆነው በትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት ከመደበኛ በታች መቀዝቀዝ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ ገልፆ፤ የሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ሆኖ ሊቆይ እንደሚችል የተተነበየ መሆኑን አስታውቋል።
የወቅቱ ዝናብ አጀማመር በደቡብ አጋማሽ አካባቢዎች ላይ መደበኛ ሁኔታውን ተከትሎ እንደሚጀምር የተመላከተ ሲሆን ÷መውጫው ላይ ግን ዝናቡ ቀድሞ ሊወጣ እንደሚችል የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
በአጠቃላይ በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የቦረናና ጉጂ ዞኖች፤ ሲዳማ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች መደበኛ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን÷ የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍል ደግሞ ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚያገኙ በትንበያው አመላክቷል።
በመሆኑም በትንበያው መሰረት የሚመለከታቸው አካላትና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማደረግ እንደሚገባው ኢንስቲትዩቱ አስገንዝቧል።