ክርስቲያኖ ሮናልዶ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ልዩ ተሸላሚ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪው ክርስቲያኖ ሮናልዶ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ልዩ ተሸላሚ መሆን ችሏል።
ሽልማቱ ይፋ የተደረገው ዛሬ በሞናኮ በተካሄደው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የምድብ ድልድል ስነ ስርዓት ላይ ሲሆን፥ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ያሳለፈው ስኬታማ ጊዜ ለሽልማቱ እንዳበቃውም ተገልጿል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ከሪያል ማድሪድ ጋር አራት ጊዜ እንዲሁም ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር አንድ ጊዜ በድምሩ አምስት ዋንጫዎችን አሳክቷል።
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲና ሮበርት ሌዋንዶውስኪን በማስከተል በ14ዐ ጎሎች የሻምፒየንስ ሊጉ የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪም ነው።
ክርስትያን ሮናልዶ በሰባት የሻምፒየንስ ሊግ የውድድር አመታት ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቅ የቻለም ሲሆን፥ በሶስት የሻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታዎች ላይ ጎል በማስቆጠር ብቸኛው ተጫዋች ነው።