ጤና ሚኒስቴር የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ ሰነድ ለብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስረከበ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጤና ሚኒስቴር የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ አካባቢያቸው በመመለስ እንዲቋቋሙና ወደ ሰላማዊ የሲቪል ኑሯቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የሚረዳ ሰነድ ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጋር የርክክብ መርሐ-ግብር አካሄደ፡፡
ሚኒስቴሩ የሳይኮሶሻል ድጋፍ አገልግሎት ላይ የጤና ምክር አገልግሎት በመስጠት የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም፣ ጤናማ የመቋቋሚያ ዘዴዎችን እንዲማሩ፣ የስነ-አዕምሮ ጤና ምክር እና አገልግሎት እንዲያገኙ በማመቻቸት ከማህበረሰቡ ጋር መስተጋብር እንዲፈጥሩ የማድረግ ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
በዚህም የሳይኮሶሻል ድጋፍና አገልግሎት ላይ በባለሙያዎች የተዘጋጀ የስልጠና መመሪያን ለብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የማስረከብ መርሐ-ግብር ተካሂዷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ÷ ችግሮችን በውይይት ፈትቶ ታጣቂዎችን ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ስራ እንደ ሀገር ትልቅ አሻራ የሚጣልበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሳይኮሶሻል ስልጠናው የቀድሞ ታጣቂዎች መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጡ የሚያስችል ከመሆኑም በተጨማሪ አምራች ዜጎች እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል፡፡
በመጀመሪያ ዙር በትግራይ ክልል የሚገኙ የቀድሞ ታጣቂዎችን ለማሰልጠን የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ለታጣቂዎቹ ከሚሰጠው ስልጠና በተጨማሪ የጤና ጉዳት ላጋጠማቸው የሕክምና አገልግሎት እንደሚመቻችም ተጠቁሟል፡፡