በፍቅረኛዋ አካል ጉዳት የደረሰባት አሜሪካዊት እንስት በፓሪሱ ፓራሊምፒክ…
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀድሞ ፍቅረኛዋ ድብደባ ምክንያት አንድ አይኗን ያጣችውና እግሮቿ የማይታዘዙላት አሜሪካዊቷ ትሬሲ ኦቶ በፓሪሱ ፓራሊምፒክ ውድድር ሀገሯን ወክላለች፡፡
የ28 ዓመቷ ትሬሲ ኦቶ ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ÷በፈረንጆቹ 2019 ከቀድሞ ፍቅረኛዋ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች መቀጠል ባለመቻላቸው መለያየታቸውን ትናገራለ፡፡
ይህን ተከትሎም የቀድሞ ፍቅረኛዋ እሷንና ቤተሰቦቿን እገድላችኋለሁ በሚል ሲያስፈራራና ሲዝት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
በማስፈራራት ብቻ ያልቆመው የቀድሞ ፍቅረኛዋ ከዕለታት አንድ ቀን ኦቶን ለመግደል በማሰብ ሽጉጥ እና ስለታም ነገሮችን ይዞ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ይገባል፡፡
ከዚያም በቀድሞ ፍቅረኛው ትሬሲ ኦቶን ላይ በመጨከን በተደጋጋሚ ፊቷን በቡጢ ከደበደበ በኋላ በያዘው ሽጉጥ ግራ አይኗ እና እግሯ ላይ በመተኮስ ከባድ ጉዳት አድርሶባታል፡፡
በዚህም ትሬሲ ኦቶ እግሮቿ መራመድ ባለመቻላቸው “ፓራላይዝ” የሆነች ሲሆን÷ ወንጀሉን የፈጸመው የቀድሞ ፍቅረኛዋም የ40 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል፡፡
በደረሰባት የአካልና የሥነ-ልቦና ድጋፍ አስቸጋሪ ጊዜያትን እንዳሳለፈች የምትገልጸው ትሬሲ ኦቶ÷በዊልቼር ላይ በመሆን የቀስት ውርወራ ስፖርት ስትለማመድ መቆየቷንና ስፖርቱን ለመዝናናት ስትጠቀምበት እንደነበር አስረድታለች፡፡
በብርታቷ የቀጠለችው ትሬሲ ባልጠበቀችው መልኩ በፓሪሱ የፓራሊምፒክ ውድድር በቀስት ውርወራ ስፖርት ሀገሯን እንድትወክል ከአሜሪካ ፓራሊምክ ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦላታል፡፡
በጥሪው መገረሟን የገለጸችው ትሬሲ “ከሞት አልጋ በበፓሪሱ ፓራሊምፒክ ውድድር ሀገርን እስከመወክል ድረስ በሕይወቴ አስደናቂ ጉዞን አድርጌያለሁ” ብላለች፡፡
“አሁን ላይ ከበርካታ አስከፊ ጊዜያት በኋላ ሕይወቴ የበለጠ በቀለማት እና በፍቅር የተሞላ ነው” የምትለው ትሬሲ ኦቶ በፓራሊምፒክ ውድድር ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ማቀዷን ተናግራለች፡፡