Fana: At a Speed of Life!

የአየር መንገዱን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል በተባሉ 6 ግለሰቦች ላይ የምርመራ ማጣሪያ የ14 ቀን ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል ተብለው በተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች ላይ የምርመራ ማጣሪያ የ14 ቀን ፈቅዷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ትናንት ከሰዓት በኋላ በዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል) ጊዜ ቀጠሮ መዝገብ የተካተቱ 6 ግለሰቦች ላይ የፌደራል መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን የጥርጣሬ መነሻ እና በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል የተነሱ የመከራከሪያ ነጥቦችን መርምሮ ነው ዛሬ ተጨማሪ ምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ለፖሊስ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን በማመን የ14 የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ለፖሊስ የፈቀደው።

በዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን ፣ ኤልያስ ድሪባ ፣ ይዲድያ ነጻነት እና እሌኒ ክንፈ በተባሉ ግለሰቦች ላይ ነው ምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ የተፈቀደው።

የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ፖሊስ  ተጠርጣሪዎቹ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ ለጉዞ በተዘጋጀ አውሮፕላን ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲቪል አቪዬሽን ሕግና አሰራር በመጣስ፣ የአየር መንገዱን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል፣ የደህንነት ባለሙያዎችን በተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረጽ አየር መንገዱ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ጠቅሶ የጥርጣሬ መነሻውን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ማቅረቡ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል ደንበኞቻቸው በዕለቱ ለጉዞ ወደ መቐለ ለመሄድ በተዘጋጁበት ወቅት በረራው በመዝግየቱ ተበሳጭተው የተፈጠረ አለመግባባት እንጂ የሽብር ተልኮ ይዘው አይደለም የሚልና ፖሊስ ያቀረበው የጥርጣሬ መነሻ የሽብር ተግባሩን የማያሟላ እና የፍሕ ፖሊስንና የወንጀል መርሕን ያልተከተለ ነው የሚል የመከራከሪያ ነጥብ አቅርበው ነበር።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ጅምር የፖሊስ የምርመራ መዝገብን በማስቀረብና በመመልከት እንዲሁም ተጠርጣሪዎቹ ቅዳሜ ዕለት በመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ በተመሳሳይ ቀርበው የ20 ሺህ ብር ዋስ ስለመፈቀዱ የሚገልጽ ማረጋገጫ በጠበቆች እንዲቀርብ በማለት ማረጋገጫውን ተመልክቶ ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ፖሊስ ሁከትና ብጥብጥ ማስነሳት መዝገብ መቅረባቸው እንጂ በሽብር ወንጀል በፌደራል ፖሊስ በኩል ያልቀረቡ መሆኑን አረጋግጧል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ በተጠርጣሪዎች ላይ ለተጀመረው ምርመራ ማጣሪያ ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግ በማመን የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.