በሲዳማ ክልል ከ1 ሺህ 800 በላይ ተወካዮች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንደሚሳተፉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል ከ1 ሺህ 800 በላይ ተወካዮች በአጀንዳ አሰባሰብ የምክክር መድረክ ላይ እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረክ በነገው እለት በሲዳማ ክልል እንደሚጀምርም ገልጿል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር)÷ በአጀንዳ አሰባሰቡ በክልሉ ከሚገኙ 45 ወረዳዎች የተመረጡ ከ900 በላይ የሚሆኑ የማህበረሰቡ ወኪሎች፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አካላት፣ ተቋማትና ማህበራት እንዲሁም ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ከ1 ሺህ 800 በላይ ተወካዮች በአጀንዳ አሰባሰብ የምክክር መድረክ ላይ እንደሚሳተፉም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የክልሉ ማህበረሰብ ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ መግባባት እንዲደረግባቸው ያስፈልጋል የሚሉዋቸውን መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች የያዙ አጀንዳዎች በህዝባዊ ውይይት ይሰበሰባልም ተብሏል፡፡
አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ ከነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት የሚደረግ ሲሆን÷ በሂደቱ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በንቃት እንዲሳተፉም ጥሪ ቀርቧል፡፡
ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ በቤንሻጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተመሳሳይ የምክክር መድረክ አካሂዶ አጀንዳዎችን ማሰባሰቡ ይታወሳል፡፡
በጀማል ከድሮ፣ ታመነ አረጋና ፍቅርተ ከበደ