የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት የ19 ሚኒስትሮችን ከሀላፊነት ማንሳታቸው ተሰማ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ካይስ ሰዒድ በመጪው ጥቅምት ወር ላይ ከሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አስቀድሞ 19 ሚኒስትሮችን ከሀላፊነት ማንሳታቸውን አስታውቀዋል።
ከሀላፊነት ከተነሱት መካከል የውጭ ጉዳይ፣ የመከላከያ እና የጤና ሚኒስትሮች እንደሚገኙበት ተገልጿል።
የቱኒዚያ ፕሬዚዳንት ሚኒስትሮቹን ከሀላፊነት ለማንሳት ውሳኔ ላይ የደረሱበት ምክንያት ምን እንደሆነ ያልገለጸው የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት መረጃ፤ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መንግስታዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ስለመወሰናቸውን ብቻ ጠቅሷል።
ፕሬዚዳንቱ ኢመድ ሜሚችን በመተካት ካሊድ ሴሂሊንን አዲስ የመከላከያ ሚኒስትር አድርጎ ሲሾሙ፥ መሐመድ አሊ ናፍቲ ደግሞ ናቢል አማርን በመተካት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ሙስጠፋ ፈርጃኒ አዲሱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው አሊ ምሬትን ተክተዋል ነው የተባለው።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፕሬዚዳንቱ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ሃቻኒን ከስልጣን በማንሳት ካሜል ማዱሪን መሾማቸው ይታወሳል።
ፕሬዚዳንቱ በመጪው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ የአምስት ዓመት የስልጣን ዘመን እንደሚፈልጉ የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡