ለአርባምንጭ ሁለገብ ስታዲየም ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአርባምንጭ ሁለገብ ስታዲየም ግንባታ የመሠረት ድንጋይ በዛሬው ዕለት ተቀምጧል፡፡
የመሠረት ድንጋዩን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እና የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ አስቀምጠዋል።
የሚገነባው ስታዲየም ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ጨዋታዎችን የሚያስተናገድ የፊፋንና የካፍን ስታንዳርድ የሚያሟላ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ስታዲየሙ ከ2 ነጥብ 43 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ ሲሆን ÷የመጀመሪያው የግንባታ ሒደት 17 ሺህ ሰው የሚይዝና 16 ሜትር ከፍታ እንደሚኖው ተመላክቷል፡፡
ወ/ሮ ሸዊት÷ስታዲየሙ የተለያዩ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን እንዲያስተናገድ ተደርጎ እንደሚገነባ ገልጸው ይህም የስፖርት ቱሪዝምን ለመሳብ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው÷የክልሉ መንግስት ለስታዲየሙ ግንባታ 500 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የበለጸገ ማህበረሰብ ለመፍጠር የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ማጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በተያያዘም ዛሬ ማለዳ ላይ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋሞ ዞን ሲቀላ ቀበሌ ባስገነባው አደባባይ ለስታዲየሙ ግንባታ ገቢ ማሰባሰብን አላማ ያደረገ የማስ ስፖርት መርሐ-ግብር ተካሒዷል።