በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 615 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኝ ተተክሏል- ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር 615 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኝ መተከሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መጠናቀቁን ተከትሎ ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የዛሬ ጀምበር ወጥታ እስክትጠልቅ 600 ሚሊየን ችግኞችን ልንተክል ኢትዮጵያውያን ሁሉ አቅደን ነበር። ያሰብነውን ሳናሳካ ጀምበር የሚጠልቅብን አይደለንምና በአንድ ጀምበር 615 ነጥብ 7 ሚሊየን ችግኞችን መትከል ችለናል።
ህፃናት ተስፋቸውን ተክለዋል። ወጣቶች ጽናተቸውን አሳይተዋል። አረጋውያን ውርስ አኑረዋል። ኢትዮጵያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከቤታቸው ወጥተው የማይደበዝዝ አሻራ አኑረዋል።
በማበራችን እና በመጽናታችን በአለም በሌላ ስፍራ በአንድ ጀምበር ያልተደረገውን እኛ ኢትዮጵያውያን አድርገነዋል።
ዛሬ ለአየር ንብረት ለውጥ ሚዛን ጥበቃ ቆመን ውለናል።
የአፈር መራቆትን ለመመከት ተሰልፈን ውለናል።
የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ስንደክም ውለናል።
ምድራችንን አረንጓዴ ለማልበስ ልምላሜን ለመመለስ ሳንበገር ሰርተናል።
ፈጣሪም ረድቶን ለዛሬዋ ጀምበር ያሰብነውን አሳክተናል።
ዛሬ 29 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች በ318 ነጥብ 4 ሄክታር በጂኦስፓሻል መረጃ በተገኘባቸው ስፍራዎች ላይ ችግኞችን ተክለዋል።
እስካሁን በመረጃ ቋት ከተመዘገበው ውጭ የተተከሉ ችግኞች መረጃ በተከታታይ የሚገለፅ ይሆናል።
ለአስደማሚው የኢትዮጵያውያን ኅበረት እና ጽናት እነሆ ምስጋና።
ለስኬታችን የእቅድ፣ የክትትል እና የመረጃ አውታር በመሆን በትጋት የሰራችሁ አመራሮች ባለሞያዎች እና የሚዲያ ተቋማት ምስጋና ይገባችኋል።
ምኞት ተግባራችን ሁሉ የተሻለች ኢትዮጵያን በኅብረት ገንብቶ ማቆየት ነው። ይኽንኑ እንቀጥላለን።