Fana: At a Speed of Life!

የዛሬን ችግር ሳይሆን የነገን ፍሬ አሻግረን በማየት ለመጪው ዘመን ብሩህነት በጋራ መስራት አለብን- ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የዛሬን ችግር ሳይሆን የነገን ፍሬ አሻግረን በማየት ለመጪው ዘመን ብሩህነት በጋራ መስራት አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የአረንጓዴ አሻራ መርኸ-ግብር የኢትዮጵያ መጻኢ ጊዜ ብሩህ እንዲሆን መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሀገሩን የሚወድ ትውልድ ከዛሬ ባሻገር ነገን አሻግሮ በማየት በትብብር እንደሚሰራ ጠቅሰው÷ በአረንጓዴ አሻራ መርኸ ግብር እየተመዘገበ ያለው ስኬትም ይህንን የሚያረጋግጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም የዛሬን ችግር ሳይሆን የነገን ፍሬ አሻግረን በማየት ለመጪው ዘመን ብሩህነት በጋራ መስራት አለብን ነው ያሉት፡፡

ከትናንት ታሪክ ትምህርት በመውሰድና ዛሬ ላይ በርትተን በመስራት ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር ማስረከብ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በመንግስት የተጀመሩ ወደ 20 የሚጠጉ የልማት ኢኒሼቲቮች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ጠቁመው÷ የአቅመ ደከማ ዜጎች ቤት እድሳት፣ የተማሪ ምገባ፣ የስንዴ ልማትና መሰል ኢኒሼቲቮችን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን ባለው ሒደት 39 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ነው ያስረዱት፡፡

በዛሬው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የተከልናቸውን ችግኞች ሲደመሩ ወደ 40 ቢሊየን ይደርሳሉ ሲሉም ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.