ሲዲሲ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባትን ለመስጠት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባትን በቀናት ውስጥ ለማስጀመር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ማዕከሉ ፥ በአህጉሪቱ የዝንጀሮ ፈንጣጣ የተስፋፋባቸው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ላይ ክትባት ሊሰጥ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡
በቅርቡ የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣን የዓለም የጤና ስጋት ነው ሲል ማወጁ ይታወሳል፡፡
በዚህም የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል፥ክትባቱ በቅርቡ መሰጠት እንዲቻል በአግባቡ ለማስቀመጥና ለመጠቀም መዘጋጀቱን ጠቅሷል፡፡
በአፍሪካ 19 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተጠቁ ሲሆን ፥ ከዚህ ውስጥ ከ90 በመቶው በላይ የሚሆኑት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንደሚገኙ አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በሽታው ከአንድ ሰው ወደሌላ ሰው የሚተላለፈው በንክኪ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡