Fana: At a Speed of Life!

በሀገራዊ ምክክር ወቅት ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቁ የሥነ-ምግባር መርሆዎች …

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች እና ባለድርሻ አካላት በሀገራቸው ጉዳይ ላይ መክረው የማኅበራዊ ውሎቻቸውን የሚያድሱበት ሂደት ነው፡፡

በሂደቱም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እና ባለድርሻ አካላትን በመወከል ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮች ቀጥሎ የተዘረዘሩትን የሥነ-ምግባር መርሆዎች ማክበር እንደሚጠበቅባቸው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

1. በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ አካላት አንዳቸው ሌላውን በማክበር፤ ርህራሄን በማሳየት አንደኛው ወገን ስለሌላኛው ወገን ለማወቅ መጣር፤ የተለያዩ አመለካከቶችን ለመረዳት ፈቃደኛ መሆን፤

2. በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ አካላት አንዳቸው ሌላኛውን ወገን ከማንኳሰስና የስነ-ልቦና የበላይነትን ለመያዝ ከመሞከር ይልቅ በሰው ልጅ እኩልነት በጥብቅ ማመን፤

3. በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላትን፣ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ስብዕናቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ ተቃውሞ እና ትችትን ከመሰንዘር በመቆጠብ በሐሳብ እና በርዕዮተ-ዓለም ደረጃ ሐሳብ ማቅረብ፤

4. በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት የማኅበረሰቡን እሴቶች ባከበረ መልኩ የምክክሩን ሂደት ማስኬድ፤

5. በሂደቱ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት የምክክር ሂደቶቹ ውስንነቶች እንሚኖራቸው በመረዳት ከግልፍተኝነት በፀዳ መልኩ ሌሎች ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መሳሪያዎችን የሂደቱ አጋዥ አድርገው ለመጠቀም ፈቃደኛ መሆን የሚሉት ናቸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.