ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከልና ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥ በጋራ መቆም ይገባል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከልና ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥ በጋራ መቆም እንደሚገባ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡
የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻን የማስቆም ብሔራዊ ጥምረት በአዘጋጀው መድረክ ላይ ሚኒስትሯ ባደረጉት ንግግር÷ በርካታ ሕጻናትና አፍላ ወጣት ሴቶችን ያለ ዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ወንጀልን በቅንጅት ታድገናል ብለዋል፡፡
በዚህ የተገኘውን አበረታች ውጤትም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመከላከል ላይ ልንደግመው ይገባል፤ ይህም የፍትሕ አካላት፣ የጤናው ዘርፍ፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሲቪክ ተቋማትና የማኅበረሰቡን የጋራ ትኩረት ይፈልጋል ነው ያሉት።
ያለ ዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም በተዘጋጀው የአምስት ዓመት ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ በመመራት ተቋማት በግልም ሆነ በጋራ ከፍተኛ ተግባር በማከናወናቸው አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያለ ዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል በሠራችው ሥራ ባለፈው ወር በተባበሩት መንግስታት እውቅና ማግኘቷ ይታወሳል።