የአየር ንብረትን በትክክል የመተንበይ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ንብረትን በትክክል የመተንበይ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የኢትዮጵያ ሜትዎሮሎጂ ኢንስቲቱዩት አስታውቋል፡፡
የኢንስቲቱዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ እንዳሉት÷በበርካታ ሥፍራዎች ከፍተኛ አቅም ያላቸው የአየር ትንበያ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ተተክለዋል፡፡
ጥራት ያላቸው መረጃዎችን የሚሰበስቡ ዘመናዊ የአየር ንብረት መከታተያ እና መቆጣጠሪያ ራዳሮችም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መገጠማቸውን አንስተዋል፡፡
ከዓለም የሜትዎሮሎጂ ድርጅት ጋር የሳተላይት መረጃዎችን የመለዋወጥ ባህል እየዳበረ መምጣቱንም ነው የገለጹት፡፡
ለሰው ኃይል አቅም ግንባታም ልዩ ትኩረት በመሰጠት እየተሰራበት እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡
ኢንስቲቲዩቱ የአደጋ ስጋት ያለባቸውን ስፍራዎች በመለየት የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ ኢንስቲቱዩቱ የአየር ንብረትን በትክክል የመተንበይ እና የአደጋ ስጋት ያለባቸው ሥፍራዎችን በመለየት አስተማማኝ መረጃዎችን የመስጠት አቅም እያደገ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
በተለይም አርሶና አርብቶ አደሩ በየጊዜው ከኢንስቲቲዩቱ የሚሰጡ መረጃዎችን ጥቅም ላይ እያዋሉ እንደሚገኙ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡