Fana: At a Speed of Life!

ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የሚሆን የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ድጋፍ የሚሆን 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ እና መድሃኒት ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ድጋፉን ያደረገው የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት(ዩኒሴፍ) ሲሆን÷ድጋፉ በአፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ትግራይ ክልሎች በሚገኙ ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ተደራሽ ይደረጋል ተብሏል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በርክክብ መርሃ ግብሩ÷የተደረገው ድጋፍ በጤና ሚኒስቴር እና በዩኒሴፍ እየተተገበረ የሚገኘው ኬር ፎር ሄልዝ ፕሮግራም አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህኛው ዙር 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የጤና መረጃ ስርአትን የሚደግፉ ኮምፒውተሮች እና ታብሌቶች፣ ለጨቅላ ህጻናት ፣ለእናቶች እና ለአፍላ ወጣቶች ጤና እንክብካቤ የሚያገለግሉ ቁሳቁስና መድሃኒቶች ድጋፍ መደረጉን ገልፀው ለፕሮጀክቱ ማስፈጻሚያ በአጠቃላይ 20 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ መገኘቱም ተገልጿል፡፡

የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ አቡበከር ካምፖ÷ድጋፉ የጤና ስርአትን በማሻሻል ጉዳት የደረሰባቸውን የኅብረተብ ክፍሎች ለመደገፍ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከዩኒሴፍ ጋር በትብብር መስራቱን እንዲቀጥል መልእክት ያስተላለፉት አቡበከር ካምፖ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፉን በገንዘብ ለደገፈው አውሮፓ ህብረት ምስጋና ማቅረባቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.