በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኝ የመትከል ዕቅድ እንዲሳካ ክልሎች ዝግጅት ማድረጋቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የተያዘው በአንድ ጀምበር 600 ሚሊየን ችግኝ የመትከል ዕቅድ እንዲሳካ የተለያዩ ክልሎች ዝግጅት ማድረጋቸውን ገለጹ።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአካባቢ ጥበቃና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ሚኒስትሮች ገለጹ፡፡
ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 600 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጥሪ፤ ህብረተሰቡ በነቂስ በመውጣት ችግኞችን በመትከል ለሀገር ያለውን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለውን ስጦታ በተገቢው ስፍራ ይገልጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አዲስ ታሪክ መስራቷን አስታውሰዋል።
በዚህ ዓመትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ነሐሴ 17 ቀን ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተካላ መርሐ ግብር፤ በክልሉ አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ በበኩላቸው በክልሉ ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ስኬት ሁላችንም ተዘጋጅተናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ በድሬደዋ ከተማ አስተዳዳር በአንድ ጀምበር አንድ ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፤ በአራት ክላስተሮችና በዘጠኝ ወረዳዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በዕለቱ በነቂስ ወጥተው አሻራቸውን እንዲያሳርፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ ለነሐሴ 17 የአንድ ጀምበር የችግኝ የተከላ መርሃ ግብር ዜጎች በነቂስ ወጥተው አሻራቸውን እንደሚያሳርፉ ተናረዋል።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በስኬት መቀጠሉን ገልጸው፤ በአከባቢ ጥበቃ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ነሐሴ 17 በሚከናወነው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ሁሉም እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።