በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርሰናል በሜዳው ከዎልቭስ ዛሬ ይጫወታል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2024/25 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ ከቀኑ 11 ሠዓት ላይ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
በዚሁ መሠረት አርሰናል በሜዳው ዎልቭስን ሲያስተናግድ÷ ኤቨርተን ከብራይተን፣ ኖቲንግሃም ፎረስት ከቦርንማውዝ እና ኒውካስል ከሳውዝሀምፕተን በተመሳሳይ ሠዓት ይጫወታሉ፡፡
እንዲሁም በአዲሱ አሰልጣኝ አርኔ ስሎት የሚመራው ሊቨርፑል ወደምስራቅ እንግሊዝ አቅንቶ በፖርትማን ሮድ ኢፕስዊች ታውንን ከሜዳው ውጭ ከቀኑ 8፡30 ይገጥማል፡፡
በሌላ በኩል ዌስትሀም ዩናይትድ አስቶን ቪላን ከምሽቱ 1፡30 ላይ በለንደን ስታዲየም ያስተናግዳል፡፡
ፕሪሚየር ሊጉ ትናንት ሲጀመር ማንቼስተር ዩናይትድ ፉልሃምን 1 ለ 0 በመርታት ጉዞውን በድል ጀምሯል፡፡
የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ነገ ከምሽቱ 12፡30 በለንደን ከተማ ስታምፎርድ ብሪጅ ላይ ቸልሲን ከሻምፒዮኑ ማንቸስተር ሲቲ ያገናኛል፡፡
የመጀመሪያው ሳምንት መርሐ-ግብር ሰኞ ሲቀጥል ቶተንሀም ሆትስፐርስ ወደ ኪንግ ፓወር ስታዲየም አቅንቶ ሌስተር ሲቲን ከምሽቱ 4፡00 ይገጥማል፡፡