የአጥንት መሳሳት መከላከያ መንገዶች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአጥንት መሳሳት ህመም በተለያዩ ምክንያቶች የአጥንት ይዘትና ክብደት መቀነስ ሲያጋጥም የሚፈጠር ህመም ነው፡፡
የአጥንትና የመገጣጠሚያ ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ጸጋ ይልማ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የአጥንት መሳሳት የሚባለው የአጥንት ይዘት ማለትም የካልሽየምና የሌሎች ንጥረነገሮች መቀነስና የአጥንት ክብደት መቀነስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአጥንት መሳሳት በእድሜ ከጊዜ በኋላ የሚመጣ እና በወጣትነት እድሜ በተለያዩ በሽታዎች መጠቃት ምክንያት፣ በሆርሞን መዛባት፣ ስቴሮይድን በመጠቀም እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሊመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የአጥንት መሳሳት በአብዛኛው ጊዜ የሚከሰተው በእድሜ ምክንያት(እድሜ እየገፋ ሲሄድ)መሆኑንም ነው ባለሙያዋ ያስረዱት፡፡
ዶክተር ጸጋ የአጥንት መሳሳት ምልክቶች ናቸው ብለው ከጠቀሷቸው ዋናዋናዎቹ የእጅ፣የዳሌና የአከርካሪ አጥንት ስብራቶች ይጠቀሳሉ፡፡
የአጥንት መሳሳትን ለመከለከል የአጥንት ጥንካሬን የሚያበለጽጉ ካልሺየምና ቪታሚን ዲ የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮችንና ቪታሚኖችን መውሰድ፣የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ስቴሮይድን ብዙ ጊዜ ከመጠቀም መቆጠብ፣ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያዋ ይመክራሉ፡፡