የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የላኪዎችን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የመለሰ ነው – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የላኪዎችን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የመለሰና በዘርፋ ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚያስችል ነው ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
በ2016 በጀት አመት የወጪ ንግድ አፈፃፀም፣ በ2017 በጀት አመት የወጪ ንግድ ዕቅድ እንዲሁም የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ረቂቅ መመሪያ ላይ ከላኪዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር)÷ በ2016 በጀት አመት ከአጠቃላይ ወጪ ንግድ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ገልፀዋል።
በሚኒስቴሩ ክትትል ከሚደረግባቸው ምርቶች 907 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ጠቅሰው÷ በዚህም የእቅዱን 82 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ አስረድተዋል።
ከ2015 በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ57 ነጥብ 62 ሚሊየን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የላኪዎችን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የመለሰና በዘርፋ ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ገልፀው፤ ለአፈፃፀሙ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ በበኩላቸው÷ የወጪ ንግድ ዘርፉ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው አመላክተዋል፡፡
በንግድ ስርዓቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመፍታት የ2017 ዕቅድን ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡