ቻይና ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል ሰጠች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ለ200 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል መስጠቷን አስታወቀች፡፡
የቻይና መንግስት ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ባመቻቸው ነጻ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑ 200 ተማሪዎች ውስጥ ለ23 ተማሪዎች በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የሽኝት መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በማስተርስና ፒኤችዲ ፕሮግራሞች ነው የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ የሆኑት።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ አማካሪ ሚኒስትር ሸን ኪንሚን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ቻይና በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራች ነው፡፡
በተለይ በትምህርት ዘርፉ ቻይና በየዓመቱ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል እየሰጠች መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ዓመትም በተለያዩ ፕሮግራሞች 200 ተማሪዎች የነጻ ትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ነው የገለጹት፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዓለም አቀፋዊነትና ስኮላርሽፕ ዴስክ ሃላፊ ኢዶሳ ተርፋሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ተማሪዎቹ በቻይና ቆይታቸው በሚያገኙት እውቀት የኢትዮጵያን ቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያሳድጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ