Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሰጡኝ እውቅና እና ምስጋና ተደስቻለሁ – አትሌት ታምራት ቶላ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሰጡኝ እውቅና እና ምስጋና ተደስቻለሁ ሲል በፓሪስ ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ታምራት ቶላ ገለጸ፡፡

በፓሪስ ኦሊምፒክ ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ የእውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር በተካሄደበት ወቅት አትሌት ታምራት÷ ጉዳት ላይ በመሆኑ በማራቶን የመወዳደር እድሉን ለሰጠው አትሌት ሲሳይ ለማ ምስጋና አቅርቧል፡፡

አትሌት ሲሳይ ለማ ከግለሰብ ጥቅም ይልቅ የሀገርና የሕዝብ አደራ በማስቀደም የወሰነው ነው ሲልም ለአትሌቱ ያለውን ክብር ገልጿል፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ÷ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወደ ቀደመ ከፍታው እንዲመለስ ችግሮችን በመለየት አስቸኳይ የእርምት እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

አትሌቶቹ በውድድሩ በነበራቸው ተሳትፎ የአቅማቸውን ጥረት በማድረግ ለኢትዮጵያ ሜዳሊያዎችን በማምጣታቸው ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው ታምራት ቶላ ‘እኔ ታምሚያለሁ አንተ ተወዳዳር’ በማለት የግል እድሉን ለኢትዮጵያ ውጤት ሲል የሰጠው አትሌት ሲሳይ ለማ ክብርና ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

አትሌቲክስ ኢትዮጵያ በዓለም እንድትታወቅ ያስቻለና ስፖርቱ ከሕዝብ ጋር ጥብቅ የስሜት ቁርኝት ያለው መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ አንስተዋል።

በፓሪስ ኢሊምፒክ የተደረገውን ውድድር ኢትዮጵያዊያን በቅርበት መከታተላቸውን ገልጸው÷ በውድድሩ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አለመመዝገቡን አንስተዋል።

የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት ሶስት ተከታታይ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ 1 የወርቅ ሜዳሊያ ብቻ መገኘቱ ያሉትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት አፋጣኝ የእርምት እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ማመላከቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ያላት ውጤት ከዚህ በላይ እንዳይንሸራተት ቀድሞ ወደነበረበት ከፍታ እንዲመለስ ማድረግ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.