መንግስት ዜጎች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ የሰጠው ትኩረት የሚበረታታ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ የሰጠው ትኩረት የሚበረታታ መሆኑን የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ልዑክ ገለፀ፡፡
ልዑካን ቡድኑ ወደ ውጭ ሀገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች አስፈላጊውን ክህሎት እንዲያዳብሩ እያደረገ የሚገኘውን የምስራቅ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ የልዑካን ቡድኑ አባላት የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን በሥፋት ለሥራ የሚሰማሩባት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ብቁ ሠራተኞችን ለማፍራት የሚሰጠውን ሥልጠና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እንደሚሠሩ ገልፀዋል፡፡
በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የተመረጡ የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ወደ ውጭ ሀገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች አስፈላጊውን ክህሎት እንዲላበሱ የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡