Fana: At a Speed of Life!

በ2016 በጀት ዓመት አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል – ከንቲባ አዳነች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የአስተዳደሩ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ መጠናቀቁን ገልጸው÷ ዓመቱ የከተማው የገቢ አሰባሰብ አቅም 44 በመቶ ያደገበት መሆኑን እና በኮሪደር ልማት ስራዎች አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ ማድረግ የተቻለበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ተስፋ ያለመለሙ የሰው ተኮር ስራዎች የበርካቶችን ሸክም ያቀለሉበት፣ የአቅመ ደካሞችንና የሀገር ባለውለታዎችን እምባ አብሰው ማኅበራዊ ፍትሕን ያነገሱ ስራዎች የተሰሩበት ዓመት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመደጎም 11 ቢሊየን ብር ስራ ላይ መዋሉን፤ በጀትን 63 በመቶ ለልማት በማዋል የህዝብን ሀብት ከምዝበራ መታደግ መቻሉን፤ ለህዝብ ግልጋሎት ክፍት የተደረጉት ከ18 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶችም ማንንም ወደኋላ ያልተው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

17 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን ማሳደግ መቻሉንም የገለጹት ከንቲባዋ÷ ፍትሐዊና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ በ10 ተቋማት ጠንካራ ሪፎርሞች እና አሰራሮችን የዘረጋንበት እንዲሁም አቅመ ደካሞችን እና የሀገር ባለውለታዎቻችንን የደገፍንበት ዓመት ነበር ብለዋል፡፡

ከህዝብ ጋር ባደረግናቸው ውይይቶች በተለይም ሌብነት፣ ብልሹ አሰራርን እና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያለውን ውስንነት በቁርጠኝነት በማስተካከል ለህዝባችን በገባነው ቃል መሰረት የምንሰራ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ውስንነቶች ላይ አፋጣኝ እርማት እየወሰድን ጥንካሬዎቻችንን በማስቀጠል አሁንም አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ለነዋሪዎች ምቹ የሆነች ከተማ መገንባታችንን እንቀጥላለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.