Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ የተረከባቸውን ሎጅና ሪዞርቶች በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚያስገባ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ተገንብተው በስካይ ላይት ሆቴል ስር እንዲተዳደሩ የተረከቧቸው ሎጅና ሪዞርቶች በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡ የኢትዮጵያ አየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው አስታወቁ፡፡

የሀላላ ኬላ ሪዞርት፣ የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ፣ የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም እንዲሁም የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በስካይላይት ሆቴል ስር እንዲተዳደሩ መረከባቸውን አቶ መስፍን አስታውሰዋል፡፡

ሎጅና ሪዞርቶቹ በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ስታንዳርድ መሰረት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ዝግጅት መደረጉን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን እና በቀጣይ ሳምንታት ቀሪዎቹን ወደ አገልግሎት ለማስገባት መዘጋጀታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

አየር መንገዱ ከዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ባሻገር የሀገር ውስጥ ትስስርን ይበልጥ እያጠናከረ መሆኑን ገልጸው÷ ይህም ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር የጎላ ሚና አለው ብለዋል፡፡

በቀጣይም የአውሮፕላን ማረፊያ በሌላቸው የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች በመሬትና በውሃ ላይ የሚያርፉ አነስተኛ የቱሪስት ማጓጓዣ አውሮፕላኖችን ወደ ስራ ለማስገባት ጥናት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.