የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) የሕግ ሰውነት ጉዳይን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ብሔራ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥር 3944/ማኮ1/644 በተጻፈ ደብዳቤ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመለስ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ቦርዱም የቀረበለትን ጥያቄ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና ይህንኑ ዐዋጅ ከአሻሻለው ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንጻር መርምሮ የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥቷል፡፡
- ፓርቲው ያቀረበውን የሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት የመመለስ ጥያቄን በተመለከተ ይኸው ጥያቄ ከዚህ ቀደም ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም እና ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ለቦርድ ቀርቦ ቦርዱም ጥያቄውን መርምሮ በዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት የቀድሞውን የፓርቲውን ሕልውና መመለስ የሚያስችል የሕግ ድንጋጌ የለም በማለት ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም ወኗል፡፡ ውሣኔውንም በወቅቱ አሳውቋል፡፡ በሌላ በኩል ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011ን ያሻሻለው ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 በዓመፅ ተግባር ተሠማርቶ ለተሠረዘ ፓርቲ የቀድሞውን ኅልውና መልሶ የሚሰጥ የሕግ ድንጋጌ ያልያዘ በመሆኑ ቦርዱ በድጋሚ የቀረበለትን ሕጋዊ ሰውነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሚለውን ጥያቄ አልተቀበለውም፡፡
- በዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 ማሻሻያ ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ 2 (1) አንድ የፖለቲካ ቡድን ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመፅ ተግባር ላይ የተሣተፈ እንደሆነ እና ይህንን ተግባር ማቆሙን እና ሕገ-መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ በዚሁ መሠረት የፍትሕ ሚኒስቴር በማሻሻያ ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ 2 (1) መሠረት ሰኔ 17/2016 በቁጥር ፍሚ1/1345 ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ህ.ወ.ሓ.ት ኃይልን መሠረት ያደረገ የዐመፅ ተግባሩን በማቆም ሕገ-መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ የተስማማ መሆኑን በመጥቀስ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ማሻሻያ ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀፅ 2 (1) መሠረት በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ ማረጋገጫ ለቦርዱ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪ ህ.ወ.ሓ.ት ካቀረበው ማመልከቻ ጋር በተሻሻለው ዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀፅ 2 (2) ላይ የተዘረዘሩት የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ የፓርቲ ኃላፊዎች ስምና ፊርማ የያዘ ሠነድ አቅርቧል፡፡ በመሆኑም የፍትሕ ሚኒስቴር የሰጠውን ማረጋገጫ እና ህ.ወ.ሓ.ት ያቀረባቸውን ከላይ የተገለጹትን ሠነዶች መሠረት በማድረግ ህ.ወ.ሓ.ት በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ ቦርዱ ወሥኗል፡፡ የሚሰጠውም የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ በዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 ላይ በተደነገገው መሠረት በልዩ ሁኔታ የሚል ቃል ያለበት ሆኖ እንዲዘጋጅ ቦርዱ ወሥኗል፡፡
- ቦርዱም በዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ ሦስት መሠረት ይህ በልዩ ሁኔታ የመመዝገብ ውሣኔን የያዘው ደብዳቤ ለፓርቲው ከደረሰው ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራቶች ውስጥ ፓርቲው የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርግ፤ በዚህ ጉባዔም መተዳደሪያ ደንቡን እንዲያፀድቅ፣ አመራሮቹን እንዲያስመርጥ ቦርዱ ወሥኗል፡፡ የቅድመ ጉባዔ ዝግጅት የተመለከቱ ሥራዎችን ቦርዱ መከታተል እንዲችል ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ከማድረጉ 21 ቀናት በፊት የጠቅላላ ጉባዔ የሚያደርግበትን ቀን ለቦርዱ ማሳወቅ አለበት።
- ጠቅላላ ጉባዔው በቦርዱ ከፀደቀ በኋላ ባሉት የአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ውስጥ ፓርቲው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆን አለመሆኑ በዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ 3 መሠረት ክትትል የሚያደርግ መሆኑ ቦርዱ ወሥኗል፡፡
- በመጨረሻም ቦርዱ የሰጠውን ውሣኔ የሚገልፅ ሁለት ገጽ በቀን ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥር አ1162/11/15180 የተጻፈ ደብዳቤና በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ስለመመዝገቡ የተሰጠው የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ለህ.ወ.ሓ.ት እንዲደርሰው ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
አዲስ አበባ
ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም