Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ላቀረበችው ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ የዓለም ንግድ ድርጅት የአክሴሽን ዲቪዥን ዳይሬክተር ማይካ ኦሺካዋ ገልጸዋል፡፡

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከማይካ ኦሺካዋ ጋር በኢትዮጵያ የአባልነት ድርድር ሂደት ዙሪያ መነጋገራቸውን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ጥያቄ ካቀረበች ረዥም ጊዜ የሆናት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተገበረቻቸው ያሉ በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የድርድር ሂደቱን በተሻለ ፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደሚያግዙ ማብራራታቸውን አመልክተዋል፡፡

ስለሆነም በቀጣይ ለ5ኛው የስራ ቡድን ስብሰባ የሚቀርቡ ሰነዶች ወደ ተግባር የገቡ በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ያካተተ እንዲሆን ከድርጅቱ ባለሙያዎች ጋር በመከለስ ሂደት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዳይሬክተሯ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ የአባልነት ሂደት እስካሁን በማነቆነት ከሚጠቀሱ የፖሊሲ እና የህግ ጉዳዮች መካከል በቅርቡ የተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የዓለም ንግድ ድርጅት ያለ ኢትዮጵያ ተሳትፎ ሙሉ አይሆንም ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ድርድሩን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በሴክሬታሪያቱ በኩል ቴክኒካል ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚሰጥ መግለፃቸውንም አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.