ኢትዮጵያና ፓኪስታን በሠው ኃብት ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በሠው ኃብት ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በክር ከፓኪስታን የፓኪስታናዊ ባህር ማዶ ነዋሪዎችና የሠው ሃብት ልማት ሚኒስትር ሳሊክ ሁሳኢን ጋር በሁለትዮሽ፣ ክልላዊና የሠው ሃብትን ልማትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ጀማል÷ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የአምራች ኃይል ያማከለ ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም መተግበር መጀመሩን ገልፀዋል።
ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን እና ዘላቂነትን የሚደግፍ ዘመናዊ እና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ መመሥረት፤ ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢ እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ዐቅምን ማጠናከር እና ጥራት ያለው አገልግሎትን በብቃት ለማቅረብ የመንግሥትን ዐቅም ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ስለ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የበጋ የስንዴ ልማት ማብራሪያ መስጠታቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሚኒስትሩ ተቋማቸው በአሁኑ ሠዓት ወደ ውጭ ሀገር ለሚሄዱ ሠራተኞች የ3 ወር ቋንቋን ጨምሮ ስልጠና እየሠጠ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ኤምባሲው በፓኪስታን ውስጥ እያደረገ ያለው የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ አካል መሆን እንደሚፈልጉም ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ሁለቱ ሀገራት በሰው ኃብት ልማት ዘርፍ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።