Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዘመናዊ የብረት ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዘመናዊ የብረት ፋብሪካ እንደሚገነባ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ አስታወቀ።

የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ፥ ኢትዮጵያ ጥቃቅን ብሎን ሳይቀር ከውጭ እያስገባች እንደምትገኝ ጠቅሰው፤ ይህንን በማስቀረት በራስ አቅም ለመሸፈን መታቀዱን ተናግረዋል።

በዚህም በ2017 በጀት ዓመት በሀገሪቱ የመጀመሪያው እና ትልቁ ዘመናዊ የብረት ፋብሪካ በነቀምቴ ከተማ ግንባታው እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

በምዕራብ ኢትዮጵያ የብረት ማዕድን እንዳለ ይታመናል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፥ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ፋብሪካው በነቀምቴ ከተማ እንዲገነባ መንግስት ወስኗል ብለዋል፡፡

ሙሉ የፋብሪካው ግብአት ከጣሊያን ተገዝቶ ወደ ሀገር ቤት መግባቱን ጠቅሰው፥ ፋብሪካው በውስጡ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ ሦስት ፋብሪካዎች እንዳሉት ጠቅሰዋል።

ፋብሪካው የሚቀርቡለትን የብረት ማዕድናት ወደተለያዩ ምርቶች ቀይሮ እንደሚያመርትም አብራርተዋል።

ፋብሪካውን ለመገንባትም ከ70 እስከ 80 ሚሊየን ዩሮ እንደሚጠይቅ ያነሱት አምባሳደር ሱሌይማን፥ ግንባታው ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ፋብሪካው በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥርና በዓመት 90 ሚሊየን ዶላር ግምት ያለው ምርት የማምረት አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።

ይህም ከተለያዩ ሀገራት የሚገባውን የብረት ምርት ለመቀነስ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ቢሾፍቱ ላይ ከ10 ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በብልሽት ላይ የሚገኘውን የብረት ፋብሪካ በዚህ ዓመት ወደ ስራ ለማስገባት መታቀዱን ገልጸው፤ ሁለቱ ፋብሪካዎች ወደ ስራ ሲገቡ ከውጭ የሚገቡ የብረት ምርት ከመቀነስ ባለፈ በሂደት ወደውጭ ለመላክ ታቅዷልም ነው ያሉት።

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.