ከንቲባ አዳነች በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለሕዝብ መዝናኛ አገልግሎት እንዲውል የተገነባውን ፋውንቴን መረቁ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ ለሕዝብ መዝናኛ አገልግሎት እንዲውል የተገነባውን ፋውንቴን መርቀው አገልግሎት አስጀመሩ፡፡
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ እንዲሁም ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ከተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በተጨማሪ ሥራው በሌሎች የግል እና የመንግሥት ተቋማት እየተስፋፋ ነው ብለዋል፡፡
ፒያሳ ዶሮ ማነቂያ አካባቢ በብራዘርስ ኮንስትራክሽን እና ቦሌ ርዋንዳ ድልድይ ስር በአሰር ኮንስትራክሽን በራሳቸው ወጪ ለሕዝብ መዝናኛ እንዲውሉ የገነቧቸው ፋውንቴኖች ቀደም ሲል ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡
በአጠቃላይ በእነዚህ ሥራዎች ላይ ለተሳተፉት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢኮስኮ)፣ ብራዘርስ ኮንስትራክሽን እና አሰር ኮንስትራክሽን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሌሎች የግል እና የመንግሥት ተቋማትም ከዚህ ልምድ በመውሰድ አካባቢያቸውን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል::