የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው በተሟላ መልኩ መተግበሩ ከ27 ቢሊየን ዶላር በላይ ኃብት ማሰባሰብ አስችሏል ተባለ
መንግሥት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራን በተሟላ መልኩ ማስጀመሩን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) የኢትዮጵያን የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ፥ መንግሥት ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የተከማቹ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የኢኮኖሚ ስብራቱን ከመሠረቱ በመፍታት የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባትም በየጊዜው የተለያዩ ማሻሻያዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲውን በተሟላ መንገድ ገቢራዊ ማድረጓ ወቅታዊና ምክንያታዊ መሆኑንም ገልፀዋል።
ፖሊሲው በሁሉም መስኮች ውጤታማ ሥራዎችን ለማከናወንና የኢኮኖሚ ስብራቱን በዘላቂነት ለመፍታት ወሳኝ መሆኑንም አክለዋል።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ እየተደረጉ ያሉ የማሻሻያ ሥራዎች ውጤት እያስመዘገቡ ነው ብለዋል።
የፖሊሲ ትግበራውን ተከትሎ ከተለያዩ የፋይናንስ ምንጮች ከ27 ቢሊየን ዶላር በላይ ኃብት ማሰባሰብ መቻሉንም አብራርተዋል።
የተገኘው ኃብት ደሀ ተኮር ለሆኑ ተግባራትና ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሳለፍ የተያዙ ውጥኖችን እውን ለማድረግ ለሚሰሩ ሥራዎች ይውላልም ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአንድ ጊዜ አለመደረጉንና ኃብት ማፈላለግን ጨምሮ ለፖሊሲ ማሻሻያው አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም አስታውቀዋል።
በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች የተደረጉ ማሻሻያዎች የኢኮኖሚ ስብራቱን ለማሻሻል ትልቅ አቅም የፈጠሩ መሆናቸውንም ነው ያብራሩት።
የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው በተጨባጭ የዜጎችን ኑሮ የሚቀይር መሆኑን ገልጸው፤ ከትግበራው ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶችን ቀድሞ በመለየት መፍትሔ እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዋጋ ንረት ስጋትን ለመከላከል ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችና የልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚዎች በተሻለ ድጎማ እንዲያገኙ መደረጉንም ነው ያነሱት።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ እንደነበረች አስታውሰው ፥ በመንግሥት በተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ከ30 በመቶ በላይ የነበረውን የዕዳ ጫና ወደ 17 በመቶ ማውረድ ተችሏል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ አንዱ ትሩፋት የውጭ ዕዳ ጫናን መቀነስ መሆኑንም ነው ያነሱት።
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ተግባራዊ መደረጉ ኢትዮጵያ እዳዋን እንድትቀንስና እንድታሸጋሽግ በማድረግ የዕዳ ጫናውን ወደ መካከለኛ ደረጃ ማውረድ መቻሉን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የፖሊሲ ትግበራው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ እንዲሁም ወጪን በራስ ገቢ በመሸፈን ሀገራዊ ግብን ማሳካት የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን ያስችላል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ገቢራዊ መሆን ኢትዮጵያን ሲፈታተን የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በዘላቂነት በመፍታት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ የሚያስችል መሆኑንም እዮብ(ዶ/ር) አስታውቀዋል።