መንግስት በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ የአቅርቦትና የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር በቂ ዝግጅት አድርጓል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መመሪያ መውጣትን ተከትሎ በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ የአቅርቦትና የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት መንግስት በቂ ዝግጅት ያደረገ መሆኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ የዘይትና ስኳር አቅርቦትን ለማሳለጥ ከፍራንኮ ቫሉታ እና አጠቃላይ አስመጪዎች ማህበር ተወካዮች ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል ብለዋል።
የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መመሪያ መውጣትን ተከትሎ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ምርትን በማከማቸት እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነና እንደዚህ አይነት ድርጊት ከመፈፀም ነጋዴዎቹ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መመሪያ መውጣትን ተከትሎ የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር እና ገበያውን ለማረጋጋት በመንግስት በቂ ዝግጅት የተደረገ በመሆኑ መደበቅና ማከማቸት ነጋዴዎቹን ለኪሳራ የሚዳርጋቸው መሆኑን አውቀው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል፡፡
የሚኒስቴሩ መረጃ እንዳመለከተውም፤ በፍራንኮ ቫሎታ ተፈቅዶላቸው መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች በተለይም እንደ ዘይትና ስኳር የመሳሰሉ በሚያስመጡ ነጋዴዎች እና በኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሸን መካከል ከታክስ ክፍያ ጋር በተያያዘ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ዙሪያ ውይይት በማድረግ ችግሩ ተፈትቷል።
በመሆኑም ከነገ ጀምሮ በጉምሩክ ቅርንጫፍ ጣቢያዎች የተያዙ ዘይትና ስኳር ተለቅቆ ወደ ገብያ እንደሚወጣ ተገልጿል።