ትዕዛዝ አላከበሩም የተባሉ የፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል እና የእስረኞች አሥተዳደር ኃላፊዎች ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አላከበሩም የተባሉ የፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል እና የእስረኞች አሥተዳደር ኃላፊዎች ተቀጡ፡፡
የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ነው።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ፍስሀ ጀንበሩ በወንጀል ተጠርጥረው በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ፍርድ ቤት ቀርበው በተሰጣቸው የዋስትና መብት ከእስር እንዲፈቱ የታዘዘላቸው ተጠርጣሪዎችን ባለመፍታት እና የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ባለማክበር ምክንያት ተከሳሾቹን ለምን ከእስር እንዳልፈታ ችሎት ቀርቦ እንዲያስረዳ ሲታዘዝ ባለመቅረቡና ተገቢውን መልስ ባለመስጠቱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስላላከበረ በአንድ ወር እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።
እንዲሁም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የእስረኞች አሥተዳደር ኃላፊ ሳጅን ኢብራሂም አብዲሚኖኒ በጊዜያዊ የእስረኞች ማቆያ የነበሩ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በሕገ-መንግስቱ የተሰጣቸውን ከቤተሰብ ጋር የመገናኘት መብታቸው እንዲከበርና እንዲገናኙ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ ባለማክበር በአንድ ወር ደሞዝ እንዲቀጣ ተወስኗል።
በታሪክ አዱኛ