Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ክልል በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የ50 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ50 ሚሊየን ብር በላይ የዓይነት ድጋፍ አደረገ።

የክልሉ ልዑካን በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዉ፤ ለቤተሰቦቻቸዉ መጽናናትን ተመኝተዋል።

የኦሮሚያ ክልልን ወክለው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ሀላፊ ሞገስ ኢዳኤ÷ በአደጋው የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በክልሉ መንግስት ስም ገልጸው ለሁሉም ወገኖች መጽናናትን ተመኝተዋል።

በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት የኦሮሚያ ክልል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በመጀመሪያ ዙር በአይነት 50 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ ይጥላል ብለዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ በበኩላቸው÷ አደጋዉ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለመደገፍና ለማቋቋም ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀጣይም ተጎጂዎች እስከሚቋቋሙ ድረስ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.