ፋብሪካውን በባለቤትነት ስሜት ልትጠብቁትና ልትጠቀሙበት ይገባል – ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በነቀምቴ ከተማ የተገነባውን የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ በባለቤትነት ስሜት ልትጠብቁትና ልትጠቀሙበት ይገባል ሲሉ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ገለጹ፡፡
በቀዳማዊ እመቤት ጽ/ቤት ከሚገነቡ 14 የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካዎች 12ኛው ዛሬ በነቀምቴ ከተማ በይፋ ተመርቋል።
በሥነ-ስርዓቱ ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው፥ ፋብሪካው ከአሁን ወዲህ የራሳችሁ በመሆኑ በባለቤትነት ስሜት ልትጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።
አካባቢው ድንቅ የተፈጥሮ ሃብት ያለው እንደሆነ የገለጹት ቀዳማዊ እመቤቷ ፥ ይህንን ልትጠብቁ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ፋብሪካው ላለበት የተሽከርካሪ እጥረትም የቀዳማዊ እመቤት ጽ/ቤት ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ማሕበራዊ ስብራትን ለመጠገን አዲስ ባሕል አስጀምረዋል ብለዋል።
በዚህም መፅሐፍትን ለሽያጭ በማቅረብ በሚገኘው ገቢ በመላው ሀገሪቱ ትምህርት ቤቶችን አስገንብተዋል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ክልሉም ከዚህ ልምድ በመውሰድ በርካታ ትምህርት ቤቶችን ማስገንባቱን አንስተዋል፡፡
በአካባቢው ቀጣይነት ያለው የልማት ስራ እንዲረጋገጥ ክልሉ ትኩረት መስጠቱንም ነው ያነሱት።
ዛሬ በነቀምቴ የተመረቀው የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ግንባታ 95 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበታል።
በመጨረሻም ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በፋብሪካው ግቢ ውስጥ ችግኝ ተክለዋል።
በወንድሙ አዱኛ