ሰሜን ምዕራብ ዕዝ ግዳጅና ተልዕኮውን በጀግንነት እየተወጣ የሚገኝ ጠንካራ ዕዝ ነው – ጄኔራል አበባው ታደሰ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ሰሜን ምዕራብ ዕዝ በየትኛውም ጊዜና ቦታ የሚሠጠውን ግዳጅና ተልዕኮውን በጀግንነት እየተወጣ የሚገኝ ጠንካራ ዕዝ ነው ብለዋል።
ጄኔራል አበባው ታደሠ ከዕዙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በሰሜን ምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር አካል በሆነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈዋል።
በዚህ ወቅትም ጄኔራል አበባው፥ ይህንን ጥንካሬ ማስቀጠልና በቀጣይ ለሚሰጠው ግዳጅና ተልዕኮ በሁሉም መስክ የበለጠ መዘጋጀት ይጠበቅበታል ሲሉ አሳስበዋል።
የመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል በላይ ስዩም፥ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ፣ የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ግዛው ኡማን ጨምሮ ጄኔራል መኮንኖችና የጠቅላይ መምሪያው ስታፍ አባላት በችግኝ ተከላው ላይ ተሳትፈዋል።
በዕለቱም ለምግብነት የሚውሉ የፓፓዬ፣ የአቮካዶና ሌሎች የሀገር በቀል ችግኞች በክብር እንግዶቹና በጠቅላይ መምሪያው ስታፍ አባላት መተከላቸውን ከሠራዊቱ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።