ተመድ በጎርፍ ለተጎዱ ደቡብ ሱዳናውያን ድጋፍ ላደርግ ነው አለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎርፍ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ደቡብ ሱዳናውያን ድጋፍ ለማድረግ ማቀዱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ፡፡
በሀገሪቱ በጎርፍ ጉዳት ከደረሰባቸው 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎች መካከል ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ለ 2 ነጥብ 4 ሚሊየኑ ሰብዓዊ ድጋፍ ሊቀርብ መሆኑን የድርጅቱ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) አስታውቋል፡፡
ለደቡብ ሱዳን በቀረበው የሰብዓዊ ጥሪ መሰረት ከሚያስፈልገው 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ገቢ የተደረገው 542 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው መባሉን ጠቅሶ ዥንዋ ዘግቧል፡፡
ይሁን እንጅ የጎርፍ አደጋውን ጨምሮ በሱዳን ያለውን ግጭት ሸሽተው የሚሄዱ ስደተኞችን ፍላጎት ለማሟላት በሀገሪቱ ከሚደረገው ሰብዓዊ ምላሽ በተጨማሪ አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ነው ኦቻ የገለጸው፡፡