Fana: At a Speed of Life!

የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን የውሃ ሀብቶች የጋራ አጠቃቀም ላይ ተቀባይነት ያለው ተቋማዊ አሰራር ለመፍጠር ያስችላል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን በናይል ተፋሰስ ውሃ ሀብቶች የጋራ አጠቃቀምና ልማት ላይ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ተቋማዊ አሰራር መፍጠር የሚያስችል መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ዩጋንዳና ብሩንዲ ስምምነቱን አስቀድመው በሀገራቸው የሕግ አውጪ ምክር ቤት ያፀደቁ ሀገራት ናቸው።

ደቡብ ሱዳን ስድስተኛ ሀገር ሆና ስምምነቱን ማጽደቋ ስምምነቱ ወደ ሕጋዊ ተፈጻሚነት ምዕራፍ እንዲሸጋገር አድርጎታል።

ስምምነቱን የሚያስፈጽምና ሀገራት የናይል ወንዝ ተፋሰስና የውሃ ሀብቶች ጥበቃ፣ አስተዳደርና ልማት በትብብር የሚሰሩበትን ሁኔታ የሚያመቻች የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን እንደሚቋቋም በሰነዱ ላይ ተመላክቷል።

ማዕቀፉን ከፈረሙ ሰባት ሀገራት መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ወይም ስድስት ሀገራት ስምምነቱን በፓርላማ ያፀደቁ ሲሆን÷ ያጸደቁበትን ሰነድ ለአፍሪካ ሕብረት ሲያስገቡ ኮሚሽኑን ማቋቋም ይችላሉ።

የስምምነት ሰነዱ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ለረጅም ጊዜ ውይይት ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ÷ በናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አማካኝነት ኮሚሽኑ ሕጋዊ መሰረት ይዞ መቋቋሙ የናይል የውሃ ሀብትን በጋራ ማስተዳደርና ማልማት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የኮሚሽኑ መቋቋም በውሃ ሀብቶች አስተዳደርና ጥበቃ ላይ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ሕጋዊና ተቋማዊ አሰራር የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር መሰረት እንደሚጥል ጠቅሰው÷ ኢትዮጵያም የውሃ ሀብቷን በማዕቀፉ አማካኝነት በጋራ ትብብር ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላት ተናግረዋል።

በመሆኑም የስምምነት ሰነዱን ፈራሚ ሀገራት የፈረሙትን ሰነድ ለአፍሪካ ሕብረት በማስገባት ኮሚሽኑን በአጭር ጊዜ ማቋቋምና ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ መስራት አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ተቋማዊ አሰራር እንዲፈጠር አበክራ ስትሰራ መቆየቷን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የኮሚሽኑ ስራ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.