ቻይና ሙቀት የሚያመርት 4ኛ ትውልድ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ የማስፋፊያ ሥራ ጀመረች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በዓለም የመጀመሪያ የተባለውን ከፍተኛ ሙቀት አምራች አራተኛ ትውልድ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የማስፋፊያ ሥራ ጀምራለች።
የማስፋፊያው ሥራ በምስራቅ ቻይና ሻንዶንግ ግዛት በትናንትናው እለት መጀመሩም ተመላክቷል፡፡
ቻይና ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነና የአዕምሮአዊ ንብረት መብት ባለቤት የሆነችበት ፕሮጀክት በሮንግቼንግ ግዛት በዌይሃይ ከተማ ውስጥ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ በቻይና ሁዋንግ ግሩፕ፣ በስንጉዋ ዩኒቨርሲቲ እና በቻይና ብሔራዊ ኒውክሌር ኮርፖሬሽን በጋራ የለማ መሆኑ ተመላክቷል።
በዓለም የመጀመሪያው የሆነውና አራተኛው ትውልድ በመባል የሚታወቀው ይህ የኒውክሌር ጣቢያ ባለፈው ታህሳስ ወር ወደ ንግድ ስራ መግባቱ ተገልጿል።
የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ የማስፋፊያ ምዕራፍ ሌላ በሀገር ውስጥ የበለጸገ በውሃ ሃይል የሚሰራ ሶስተኛ ትውልድ ሁዋሎንግ ዋን የተሰኘውን ማመንጫ በጋዝ ማቀዝቀዝ ስርዓት ከሚሰራው ጋር በማገኛኘት ማሰራት መሆኑን የኩባንያው ምክትል ፕሬዚዳንት ዣንግ አይጁን ተናግረዋል።
ይህ ማስፋፊያ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት ያላቸው የሁዋሎንግ ዋን ሁለት ክፍሎችን ያካተተ ሲሆን÷ ማመንጫዎቹ እያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ኪሎ ዋት አቅም እንዳላቸው ዣንግ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በዓመት 20 ቢሊየን ኪሎ ዋት ሰዓት በማመንጨት የሙቀት አቅርቦቱን በ20 ሚሊየን ካሬ ሜትር እንደሚያሳድግና 600 ሺህ ነዋሪዎችንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አክለዋል፡፡
ወደፊት የተያዘው የማስፋፊያ ዕቅድም እያንዳንዳቸው ከ1 ሚሊየን ኪሎ ዋት በላይ አቅም ያላቸው በውሀ ግፊት የሚሰሩ አራት ተጨማሪ ማመንጫዎችን እንደሚጨምር መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።