የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ጉባዔ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረሃማንና የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር አወሉ አብዲን ጨምሮ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት በአዳማ እየተካሄደ ነው።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ በዚሁ ወቅት÷ ቡሳ ጎኖፋ የመረዳዳት ሥርዓት ማህበራዊ ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ ወሳኝ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም ባለፉት ዓመታት በክልሉ በቦረና፣ በባሌ፣ በምስራቅና በምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በተከሰተው ድርቅ የሰው ህይወት እንዳያልፍና ህዝቡ ራሱ በራሱ እንዲደጋገፍ ያስቻለ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከ16 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የእህልና አልባሳት ድጋፍ በማሰባሰብ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የተማሪዎች ምገባን በዘላቂነት በክልሉ ትምህርት ቤቶች በማስጀመር እስካሁን ከ5 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች የምገባ መርሃግብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል ረገድ ቡሳ ጎኖፋ የነበረው ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ እንድንሰጥ ቡሳ ጎኖፋ ትልቅ አቅም ሆኖናል ያሉ ሲሆን÷በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች 10ሺህ ኩንታል እህል መላኩን ለአብነት አንስተዋል።
አባላቱን በብዛት በማፍራት የሚሰባሰበውን የዓይነትና የጥሬ ገንዘብ ሀብት ለማሳደግ በአዲሱ በጀት ዓመት ቀዳሚ ትኩረት የተሰጠው አጀንዳ መሆኑንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።