Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ የ”ኤቲአር” አውሮፕላኖች ጥገና ለመስጠት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የአውሮፕላኖች አምራች የሆነው “ኤቲአር” እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አካል የሆነው ኤም አር ኦ የኤቲአር አውሮፕላን ጥገና እና የስልጠና አቅምን ለማሳደግ ያለመ የፍላጎት ሰነድ መፈራረማቸው ተገለፀ።

ስምምነቱ የኤቲአርን አገልግሎት በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ በማስፋት ለሀገር ውስጥ አስተዳደሮች የተሻለ ድጋፍን በመስጠት እና የገበያ እድገትን በማጎልበት ረገድ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑ ተመላክቷል።

ትብብሩ የኢትዮጵያ የጥገና እና ስልጠና ማዕከል ለኤቲአር አውሮፕላኖች የጥገና አቅምን ማጎልበት እና በቀጣናው ላሉ የኤቲአር አስተዳደሮች የመለዋወጫ አቅርቦትን በመዘርጋት ምላሽ የመስጠት ጊዜን ለመቀነስም ያግዛል ተብሏል።

አዳዲስ የኤቲአር አብራሪዎችን ከኢትዮጵያ የአብራሪዎች አካዳሚ ጋር ለማሰልጠን የትብብር መንገዶችንም እንደሚፈጥር ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ፥ ይህ አጋርነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አህጉር እና መካከለኛው ምስራቅ የአቪዬሽን ማጣቀሻ ለመሆን ካለው ራዕይ ጋር የሚጣጣም ነው ብለዋል።

አላማችን እውቀታችንን ለማጋራት እና መላው የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ አቪዬሽን ማህበረሰብን ለመጥቀም ነው ሲሉም አክለዋል።

የኤቲአር ዋና ስራ አስፈፃሚ ናታሊ ታርናውድ ላውዴ ÷የኢትዮጵያ የአውሮፕላን ጥገና እና ማሰልጠኛ ማዕከል ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸው የማስፋፊያ ሥራዎች አቅማቸውን ለማጎልበት ካደረጉት ቁርጠኝነት ጋር ተዳምሮ ለአፍሪካና ለመካከለኛው ምስራቅ የኤቲአር አስተዳደሮች የተሻለ ድጋፍ ለመስጠት እድል ይፈጥራል ብለዋል።

አክለውም ይህ ትብብር ለኤቲአር ያለውን ቀጣናዊ አቪዬሽንን እንደሚያሳደግ እና ተጨማሪ እድገትን እንደሚከፍት እርግጠኞች ነን ማለታቸውን ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.