በአማራ ክልል የወባ በሽታ ስርጭት እየተስፋፋ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የወባ በሽታ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በክልሉ የሚስተዋለውን የወባ ሥርጭት መግታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የአማራ ክልል የወባ ወረርሽኝ ያለበትን ደረጃ የሚዳስስና የወባ በሽታ መስፋፋት እና ምላሹ ምን መሆን እንደሚገባው የሚያሳዩ ሁለት ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል።
በዚህም በአማራ ክልል 34 ወረዳዎች በአስጊ የወባ ወረርሽኝ ስርጭት ላይ መሆናቸው ነው የተመላከተው፡፡
የወባ ወረርሽኙን ለመግታት ከፍተኛ የሆነ ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ መፍጠር ካልተቻለ ማህበረሰቡን የሚያጠቃበት ደረጃ ላይ መድረሱ ተነስቷል፡፡
ስለሆነም ማህበረሰባዊ ንቅናቄ በበመፍጠር ከወባ ወረርሽኙ የአካባቢውን ማህበረሰብ መታደግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
የጤና ልማትና ጸረ ወባ ማህበራት በበርካታ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የመከላከል ሥራ እያከነወኑ ቢሆንም ተጨማሪ ጉልበትና ተባባሪ ሃይል እንደሚያስፈልግምተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሃላፊነት በመውሰድ የዩኒቨርሲቲውንና የአካባቢውን ማሕበረሰብ ከወባ ወረርሽኝ ለመጠበቅ አስቸኳይ ስራ እንዲጀምር አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡