በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ስኬቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 በጀት ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶች የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 3ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ይገኛል።
የክልሉን የ2016 በጀት ዓመት የመንግስት ስራ አፈፃፀም እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ሪፖርትን ለጉባኤው ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምግብና ስነምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርናው መስክ ትልቅ አብዮት እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በ2016/17 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ 10 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማልማት 337 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በክልሉ 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል መታቀዱን ገልጸው፤ እስካሁን 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ችግኝ እንደተተከለ ተናግረዋል።
ከ290 ቶን በላይ ቡና፣ ከ6 ሺህ 600 ቶን በላይ ሻይ፣ ከ157 ሺህ በላይ ቶን አትክልትና ፍራፍሬ፣ ከ214 ሺህ ቶን በላይ ጥሬ እህል እንዲሁም ከ500 ሺህ በላይ የቁም እንስሳትን ወደ ውጭ መላክ ተችሏል ሲሉም ገልፀዋል።
ቅመማ ቅመሞች፣ ሰሊጥና ጫትን ጨምሮ በርካታ የግብርና ምርትን ለውጭ ገበያ መቅረቡን ተናግረዋል።
ገቢን ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ ተግባራት ከ123 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን በመግለጽ የክልሉን የመንገድ ሽፋን ከ61 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከ420 በላይ የጤና ተቋማት ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን፣ ከ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ዜጎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች ግንባታ ከ15 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛ፣ ከ15 ሺህ 300 በላይ አንደኛ ደረጃ እና ከ1 ሺህ 300 በላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል ብለዋል።
የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ፣ ወረርሽኞችን ለመከላከል እንዲሁም የመድሃኒት እጥረትን ለመፍታት፣ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።
3 ነጥብ 7 ሚሊየን ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሯል አቶ ሽመልስ÷ በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ በሚያስቀጥል እና ጉድለቶችን መሙላት በሚያስችል መልኩ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ መቀረፁን አመላክተዋል፡፡
በመራዖል ከድር