የአይቲ መቋረጥን ተከትሎ ከመረጃ ጠላፊዎች ተጠበቁ የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ከፍ እያሉ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትናንትናው ዕለት በዓለም ዙሪያ የጉዞ ቀውስ ያስከተለው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መቆራረጥ አሁንም መጠነኛ መስተጓጎል መፍጠሩን ቀጥሏል።
ይሁንና ክስተቱን ተከትሎ መረጃ መጥለፍ የሚፈልጉ ወንጀለኞች ሊያስከትሉ ከሚችሉት ተጨማሪ አደጋ ራስን መጠበቅ እንደሚገባ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተፈጠረው የአይቲ መቆራረጥ ኃላፊነቱን የሚወስደው የሳይበር ደህንነት መቆጣጠሪያ ተቋም “ክራውድስትራይክ” ኃላፊ ስለተፈጠረው ችግር ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
አክለውም ደንበኞች ከክፋት ተዋንያኖች እንዲጠበቁ ማስጠንቀቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ዓለም በትናንትናው ዕለት ከነበረው ግዙፍ የአይቲ አገልግሎት መቋረጥ እያገገመች መሆኗ እየተነገረ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ከአየር መንገድ እስከ የገንዘብ ተቋማት አገልግሎት ድረስ ብዙ ኢንዱስትሪዎች የተጎዱ ሲሆን÷ ለጉዳቱ ኪሣራውን ማን ይከፍላል? የሚለው ጉዳይ እያነጋገረ መሆኑ ተመላክቷል።