Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ምስጋኑ ከጣልያን የኢንተርፕራይዞችና ሜድ ኢን ጣልያን ምክትል ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚላን፣ ጣልያን ከተካሄደው የኢትዮ-ጣልያን የቢዝነስ ፎረም ጎን ለጎን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከጣልያን የኢንተርፕራይዞችና ሜድ ኢን ጣልያን ምክትል ሚኒስትር ቫለንቲኖ ቫለንቲኒ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በሀገራቱ መካከል ያለው ዘርፈ ብዙ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴዔታው፥ ለዚህም በመሪዎች ደረጃ የተደረጉ ጉብኝቶች እና ምክክሮች የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አንስተዋል፡፡

በሀገራቱ መካከል የተፈረሙ በርካታ የትብብር ስምምነቶች መኖራቸውን በማስታወስ÷ ከእነዚህ ውስጥ የ2023/2025 የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና ጣልያን መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር፣ በአቅም ግንባታ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በሚሰራበት ሁኔታም መክረዋል፡፡

የጣልያን መንግስት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የጋራ ልማት ለመካሄድ ይፋ ያደረገው የልማት ትብብር ማዕቀፍ የሆነው የማቲ ፕላን ኢትዮጵያ ቅድሚያ ተጠቃሚ እንደመሆኗ መጠን ትግበራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል ተስማምተዋል።

በሌላ በኩል ሚኒስትር ዴዔታው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ካሳዩ ኢንቨስተሮች ጋር በመገናኘት በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.