ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወኗ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዲፕሎማሲው ዘርፍ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው።
በበጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ የተሠራበት ነው ብለዋል።
በተለያዩ መድረኮች የተንፀባረቁ የኢትዮጵያ አቋሞች እና የተላለፉ ውሳኔዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ያስቻሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ለማጠናከር በበጀት ዓመቱ በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ በርካታ ጉብኝቶች መደረጋቸውንና ስምምነቶች መፈረማቸውን አስታውሰዋል።
በመሪዎች እና በሚኒስትሮች ደረጃ በተካሄዱ ጉብኝቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ያስቻሉ ከ71 በላይ ስምምነቶች መፈረማቸው ነው የተጠቆመው፡፡
በ501 መድረኮች ላይ ተሳትፎ መደረጉን ጠቅሰው÷በተመድ እና በሌሎች የባለብዙ ወገን መድረኮች የኢትዮጵያ አቋሞች በአግባቡ ማንፀባረቅ መቻሉን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ ማዕቀፍ አባል መሆኗ በበጀት ዓመቱ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረክ ትልቁ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።
ፍቃድ ለማውጣት የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ላደረጉ 395 የውጭ ባለሃብቶች ድጋፍ እና ክትትል መደረጉን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ጥምረት እንዲፈጠር ድጋፍ በማድረግ 18 ሽርክና እንዲመሠረት መደረጉንም ገልፀዋል።