የሁቲ አማፂያን በነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ፈጸሙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የየመን ሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር በምትተላለፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቀዋል፡፡
ፈጽመነዋል ያሉትን ጥቃት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስልም ይፋ አድርገዋል፡፡
በምስሉ ላይ እንደሚታየው አንዲት ትንሽ ታንኳ ወደ ነዳጅ ጫኟ መርከብ ተጠግታ በመርከቧ የግራ ክፍል ከተጋጨች በኋላ ከፍተኛ ፍንዳታ ተከስቷል፡፡
ጥቃት የተፈጸመባት መርከብ “ቺኦስ ላየን” መሆኗን አረጋግጫለሁ ያለው ቢቢሲ÷ በፈረንጆቹ ሐምሌ 2 ቀን 2024 ከሩሲያ ወደብ ቱፕሴ ተነስታ ሐምሌ 11 ቀይ ባሕር መድረሷን አስታውሷል፡፡
አማፂያኑ ካሳለፍነው ሕዳር ወር ጀምሮ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ-ሰላጤ የንግድ መርከቦች ላይ በርካታ ጥቃት ማድረሳቸው ይታወሳል።