አርጀንቲናውያን ተጫዋቾች በፈረንሳይ ተጫዋቾች ላይ የሰነዘሩት የዘረኝት ጥቃት ከፍተኛ ቁጣ አስነሳ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የዘር ሐረጋቸው ከአፍሪካ የሚመዘዝ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ላይ ያነጣጠረ የዘረኝነት ዘፈን ሲዘፍኑ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ትስስር ገፆች ከተሰራጨ በኋላ ከፍተኛ ቁጣ አስነስቷል፡፡
የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን አባላት ‹‹አስፀያፊ፣ ዘረኝነትና ጥላቻ›› የተሞላበት ድርጊትን ተመልክቶ እርምጃ እንዲወስድ ለዓለም አቀፉ እግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ ክስ አቅርቧል።
የፌዴሬሽኑ ኃላፊ ፊሊፕ ዲያሎ በሰጡት መግለጫ የአርጀንቲና ተጫዋቾችን ድርጊት አጥብቀው አውግዘው፤ ፊፋ እና የአርጀንቲና እግር ኳስ ማህበር እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
አርጀንቲና ኮሎምቢያን አሸንፋ 16ኛውን የኮፓ አሜሪካ ዋንጫን ካነሳች በኋላ አማካዩ ኤንዞ ፈርናንዴዝ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር ደስታቸውን ሲገልፁ ያጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው የፈረንሳይ ተጫዋቾች ላይ ያነጣጠረ የጥላቻና የዘረኝነት መልዕክት ያላቸው ቃላትን ይዟል።
ምስሉ “ስሙ፤ መረጃውን አድርሷቸው፤ ለፈረንሳይ ይጫወታሉ፣ ወላጆቻቸው ግን ከአንጎላ ናቸው። እናታቸው ከካሜሩን ሲሆኑ አባታቸው ደግሞ ናይጄሪያ ናቸው። ፓስፖርታቸው ግን የፈረንሳይ ነው” የሚል መልዕክት ያለው ነው፡፡
በተጨማሪም የፈረንሳዩን አጥቂ ኪሊያን ምባፔንም በተለየ ሁኔታ የሚያንቋሽሽ መልዕክት አለው ሲል የእግር ኳስ ማህበሩ ክስ አቅርቧል።
ድርጊቱን ተከትሎ ዡለ ኩንዴ እና ዌስሊ ፎፋናን ጨምሮ በቼልሲ እና ሌሎች ክለቦች የሚጫወቱ ፈረንሳውያን እና አፍሪካዊያን ጥቁር ተጫዋቾች ድርጊቱን ከመኮነን ባለፈ ከፍተኛ ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡
ፈርናንዴዝ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደክለቡ ቼልሲ ሲመለስ ከፍተኛ ውግዘት ሊገጥመው እንደሚችልም ተገምቷል፡፡
ለዚህ ማሳያ ደግሞ በቼልሲ አብረውት የሚጫወቱት አክሴል ዲሳሲ እና ማሎ ጉስቶ በማህራዊ ትስስር ገፃቸው ከጓደኝነት ዝርዝር እንዳስወጡትም ገልጸዋል።
ቼልሲ በበኩሉ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን የእንግሊዙ ደይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
በፈረንጆቹ 1984 የተመሰረተው ‹ፀረ-ዘረኝት ንቅናቄ› በበኩሉ ክስተቱን በፅኑ አውግዞ፤ ዘረኝነት በስፖርት ወይም በሌላ በማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ቦታ የለውም ብሏል።
በዚህ አስፀያፊ ተግባር ላይ ተሳትፎ ያደረጉ የአርጀንቲና ተጫዋቾች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን ፈርናንዴዝ በወቅቱ ከልክ ያለፈ የደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ በተፈጠረው ክስተት ይቅርታ ጠይቋል፡፡
“ስለተፈጠረው ሁኔታ ከልብ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ፤ ዘረኝነት እና አሉታዊ መልዕክት ያላቸው ቃላት የያዘ መልዕክት በመሰራጨቱ ምንም ሰበብ መደርደር አልፈልግም፤ በማንኛውም ሁኔታ ዘረኝነት እና አድልዎን አጥብቄ እቃወማለሁ” ሲል በሁኔታው መፀፀቱን ገልጿል፡፡
ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ በኋላ የአርጀንቲናው ግብ ጠባቂ ኤሚ ማርቲኔዝ የፈረንሳይ ተጫዋቾችን ለማበሳጨት የፈፀመውን ድርጊት ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ገብተው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡