ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የውጭ ባለሃብቶችን እየሳበች ነው – አምባሳደር ፈይሰል አልይ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የውጭ ባለሃብቶችን እየሳበች ነው ሲሉ በኳታር፣ የመን እና ኢራን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፈይሰል አልይ ገለጹ፡፡
አምባሳደር ፈይሰል፥ በኳታር ከሚገኘው ኮን ግሩፕ ጋር በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም እና የሰው ሃብት ልማት ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት አምባሳደር ፈይሰል አልይ እና የኮን ግሩፕ መስራችና ሊቀ-መንበር ሞሃመድ ረያድ እና ሄሳ ካህሊል አል ሶዋይዲ ናቸው፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ የኢትዮጵያና የኳታርን ግንኙነት ከማጠናከር አኳያ የራሱን አስተዋፅዖ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
በዚህም ኤምባሲው ከኮን ግሩፕ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የቱሪዝም መስህቦች፣ የወጭ ንግድ ምርቶች ለማስተዋወቅ እና በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት የሰው ሃብት ልማት ላይ በትብብር ለመስራት ያለመ እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡
አምባሳደር ፈይሰል እንዳሉት፥ ስምምነቱ በኢትዮጵያና ኳታር መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብርና የነበረውን ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
ስለሆነም ስምምነቱ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እና የንግድ እድሎችን በኳታር ለሚገኙ ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ለማስተዋወቅ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ በመሠረታዊነት እየቀየሩ መሆናቸውና ፕሮጀክቶቹ የተለያዩ የመስህብ ስፍራዎች፣ መልከዓ ምድሮች እና ፓርኮችን በመሠረተ ልማቶች በማስተሳሰር አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲከፈቱ መደላድል ፈጥሯል ብለዋል።
የኮን ግሩፕ መስራች እና ሊቀ-መንበር ሞሃመድ ረያድ በበኩላቸው፥ ስምምነቱ በሀገራቱ መካከል የኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጠናከር እና የዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
በዚህም የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ትኩረት በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት እንዲችሉ፣ የኳታር ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መዳረሻቸው እንዲያደርጉ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ምርቶች በኳታር ገበያ ከማስገኘት አንፃር ከኤምባሲው ጋር በትብብር ለመስራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።