የባሕር ዳር ከተማ የሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ የማጠቃለያ መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በሁሉም ክፍለ ከተሞች “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የነበረው ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ የማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፥ በክልላችንና ከተማችን ባለፈው አንድ ዓመት በሰላም እጦት ምክንያት ብዙ ዋጋ ተከፍሏል ብለዋል፡፡
በህዝቡ አርቆ አስተዋይነትና ሰላም ፈላጊነት ከጊዜ ጊዜ የሰላም ሁኔታው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው፤ በከተማው ውስጥ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ፣ ልማት እንዳይቋረጥ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚቻልበት ጊዜ አግኝተናል ሲሉ ተናግረዋል።
ሰላም ፈላጊ የሆነው የከተማዋ ነዋሪ ለሰላም ባደረገው ተግባራዊ እንቅስቃሴ 22 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር አስፓልት፣ 11 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ እና 12 ኪሎ ሜትር የመንገድ ከፈታ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል ከንቲባው።
በከተማዋ ውስጥ ባለው አንጻራዊ ሰላም ምክንያትም ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው የመንገድ ዳር የሶላር መብራቶች በከተማዋ መንገዶች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ጠቅሰው፤ የሕዝብ መናፈሻዎች ግንባታ መካሄዱን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ50 ሺህ በላይ የሥራ እድል የተፈጠረ ሲሆን ፥ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡ፣ የሌማት ትሩፋት ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውንና ባሕር ዳርን ጽዱ፣ ውብና ምቹ ከተማ ለማድረግ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ዘመናዊ የከተማ አገልግሎት ሥርዓት ለመገንባት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የመተግበር ሥራዎችም ተጀምረዋልም ብለዋል።
ይህ ሁሉ የሆነው የተሟላና ዘላቂ ሰላም በሌለበት ሁኔታ መሆኑን ያነሱት ከንቲባው፥ የተሟላ የሰላም ባለቤት መሆን ከተቻለ የበለጠ መሥራት ስለሚቻል ሰላምን ለማጽናት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሰላም ኮንፈረንሱ ዓላማ የተገኘውን ሰላም ማስቀጠልና የዘላቂ ሰላም ባለቤት በመሆን በሙሉ አቅም ልማት ላይ ለማተኮር መሆኑንም ተናግረው፤ ሰላማችን ለሌላው አካባቢና ለመላው የክልሉ ሕዝብ የሚዘልቅ እንዲሆን የሕዝቡን አንድነት ለማጽናት ነው ብለዋል።
በደሳለኝ ቢራራ