ኢትዮጵያ የብሪክስን ዓላማ ለማስረጽ በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሩሲያ ሞስኮ እየተካሄደ ባለው የብሪክስ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዮች የምክክር መድረክ ላይ እየተሳተፈች ነው፡፡
በመድረኩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ የተመራ ልዑክ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡
አምባሳደር ነብዩ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ የብሪክስን ዓላማ በማስረጽና የተዛቡ መረጃዎችን በመከላከል ረገድ ከአባል ሀገራቱ ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል።
የብሪክስን ትክክለኛ ዓላማና የአባል ሀገራቱን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዙሪያ የብሪክስ አባል ሀገራት መገናኛ ብዙኃን በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
መድረኩ በብሪክስ አባል ሀገራት መገናኛ ብዙኃን ዘንድ ተግባራዊ ትብብር እንዲጠናከር እና በዲጂታል ዲፕሎማሲ ሚና ዙሪያ ላይ የጋራ ውይይት ለማድረግ ያለመ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡